
ከብዙዎች ለብዙዎች መርሕ የሚመራው ባንካችን አሐዱ፤ ኤ አይ ለሁሉ የሚል መርሕ ካለው ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በአጋርነት መሥራት የሚያስችለውን የጋራ ስምምነት ሰነድ ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡
የአሐዱ፡ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ በዛ በንግግራቸው፤ “በቅድሚያ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከአሁን በፊትም ዛሬም ላደረገልን መልካም አቀባበል በአሐዱ፡ባንክ የቦርድ እና ሥራ አመራር አባላት ስም እያመሰገንኩ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኤ አይ (AI) እየተሠራ ያለውን ዘመኑን የዋጀ የሥራ ከባቢ አደንቃለሁ፤ “በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወሳል” እንዲሉ፤ በዛሬው ዕለት የጋራ ስምምነት ሰነድ መፈራረማችን ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍ አርኣያነት ያለው ተግባር መሆኑንም ለመግለጽ እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡
አክለውም፤ አሐዱ ትልቅ ሕልም ያለው ባንክ ነው፤ በኤ አይ (AI) በመታገዝ÷ በአግባቡ በመጠቀም እና በማስተዳደር፤ ዲጂታል ማርኬቲንግ ላይ ትኩረት በማድረግ፤ በተሻለ ፈጠራ የተሻለ አገልግሎት ለደንበኞቻችን ለመስጠት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለመድረሳችን ማሳያ መሆኑንም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው፤ “ኤ አይ (AI) ብቻውን ሀገርን ተሸክሞ ሊሔድ አይችልም፤ እንደ አሐዱ፡ባንክ ያሉ የግል ሴክተሮችም ሲጨመሩበት እንጂ፤ ለሀገራችን ኢትዮጵያ የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማበርከት በትብብር መሥራት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ከተቋማችን ኤ አይ ጋር ለፈጠረው አጋርነት አሐዱ፡ባንክን በጣም ላመሰግን እወዳለሁ” በማለት ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡