
አሐዱ፡ ባንክ የቦርድ እና የማኔጅመንት አባላት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩትን የጎበኙ ሲሆን፤ በዕለቱ የቴክኖሎጂ ሥራዎችንና የሮቦቲክስ ላቦራቶሪዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል። ጉብኝቱ በባንክ ዘርፍ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስን በመጠቀም የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የቴክኖሎጂ ትብብርን ለመፍጠር ያለመ ነው።
የአሐዱ፡ባንክ የዳሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አንተነህ ሰብስቤ፤ በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) ዘርፍ እያሳየች ያለውን እመርታ ከኢንስቲትዩቱ ጉብኝት የተረዱ መሆኑን ጠቅሰው አድናቆታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በቀጣይም አሐዱ፡ባንክ ከኢንስቲትዩቱ ጋር በሚኖሩ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዙሪያ ትብብር በማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳሬክተር የሆኑት አቶ ይታገሱ ደሳለኝ በበኩላቸው ፤ የፋይናንስ ተቋማት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት እንዲጠቀሙና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህ ጉብኝት በአገር በቀል የቴክኖሎጂ ተቋማትና በግል የፋይናንስ ዘርፉ መካከል ያለውን ትብብር ያጠናክረዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡