አሐዱ፡ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2024/25 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዘገበ! Dawit Addis November 24, 2025

አሐዱ፡ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2024/25 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዘገበ!

አሐዱ፡ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በወሳኝ መለኪያዎች ይበል የሚያስብል ውጤት አስመዘገበ፡፡ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በበጀት ዓመቱ ብር 7.88 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፤ ይኽም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ41 በመቶ እድገት አሳይቷል፤ በውጭ ምንዛሬ ግኝት ረገድም ከ88.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ ይኽም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10.3 በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡
በተመሳሳይ፤ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ ከብር 2.16 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ87 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ ባንኩ አጠቃላይ ሀብቱን ከብር 10.1 ቢሊዮን ብር በላይ በማድረስ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ57 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ከፍተኛ እመርታን አሳይቷል፡፡
በ2024/25 በጀት ዓመት ባንኩ አመርቂ አፈጻጸም በማሳየት፤ ከታክስ በፊት ብር 502.1 ሚሊዮን ትርፍ በማስመዝገብ፤ ከ2023/24 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 351 በመቶ ብልጫ ያለው እድገት አሳይቷል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ ተጨማሪ 390,000 ደንበኞችን በመመልመል እ.ኤ.አ. በሠኔ 2025 ላይ አጠቃላይ የደንበኞቹን ብዛት 1.1 ሚሊዮን አድርሷል፡፡
በአጠቃላይ፤ በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው ክንውን፤ ተቆጣጣሪው አካል ከሚያወጣቸው ለውጦች ጋር ባንካችን እንዴት እራሱን በፍጥነት እያላመደ እና ከለውጦቹ ጋር እየተራመደ፤ ይኽንንም ሲያደርግ የደንበኞቹን ቁጥር በአስተማማኝ ደረጃ እና በዘላቂነት እያሳደገ መሆኑን አሳይቶበታል፡፡