አሐዱ:ባንክ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ! Dawit Addis September 25, 2026

አሐዱ:ባንክ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ!

ባንካችን በሀገሪቱ ዘመናዊ የግብይት መዋቅር ውስጥ እጅግ አስተማማኝ የክፍያ ሥርዓት የሆነውን የመጋዘን ደረሰኝ ብድር (Warehouse Receipt Financing) የመግባቢያ ሰነድ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ጋር ዛሬ መስከረም 14 ቀን 2019 ዓ.ም ተፈራርሟል ።

በዚህ የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ወቅት የባንካችን ተጠባባቂ ቺፍ ኦፕሬሽንስ ኦፊሰር አቶ መልሳቸው ታደሰ እንደገለጹት፤ ባንካችን ቀደም ሲልም ከምርት ገበያ ጋር በክፍያና ርክክብ ሥርዓት አጋር ሆኖ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው ፤ አሁንም ባንካችን «ከብዙዎች ለብዙዎች» በሚለው መርሕ መሠረት የአርሶ አደሮችን ፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትንና የምርት አቀናባሪዎችን የፋይናንስ ተካታችነትና የብድር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የኢትዮጲያ ምርት ገቢያ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ቅድስት ሥጦታው በበኩላቸው፤ የዚህ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር ሥርዓት ዋነኛ ዓላማው አምራቾች ምርታቸውን ወደ ምርት ገበያው መጋዘን በማስገባት የሚያገኙትን የመረከቢያ ደረሰኝ እንደ አስተማማኝ ማስያዣ (Collateral) በመጠቀም ከባንኮች በቅልጥፍና ብድር የሚያገኙበት ፍትሐዊ ሥርዓት መሆኑን አስገንዝበዋል ።

የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱም፤ የባንካችን ተጠባባቂ ቺፍ ኦፕሬሽንስ ኦፊሰር አቶ መልሳቸው ታደሰ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ቅድስት ሥጦታው እንዲሁም የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአሐዱ:ባንክ ሐመር አዳራሽ ተከናውኗል ።

Write a comment
Your email address will not be published. Required fields are marked *